በጽርሐ ጽዮን ፕሮጀክት ውስጥ ከሚታቀፉ ጠቃሚ ፕሮጀክት ውስጥ አንዱ ቤተ መዘክር ነው፡፡ ይህ ቤተመዘክር የቤተ ክርስቲያኗን የረጅም ታሪክ ማስጎበኛና ማስተማሪያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከክርስትና ኃይማኖት ከተጀመረበት ጊዜ በፊት ጀምሮ ታሪክ ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ዛሬ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ በአምልኮት ስርዓት ውስጥ የሚታቀፉት ጽላቶች ከእስራኤላውያን ታሪክ ከሙሴ ዘመን ጋር በእጅጉ የተያያዙ እንደመሆናቸው ቤተ ክርስቲያኗ ይኸንን የረጅም ዘመን ታሪኳን ለዘመኑ በሚመጥን መንገድ አዘጋጅታ ትውልዱ እንዲማርበት፣ ብሎም ለመጪው ትውልድ በሚገባ ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ ተገቢውን ሃላፊነት መወጣት ይኖርበታል፡፡ ይህንን ማድረግና ዘመኑን በሚገባ መዋጀት የሚቻለው ዘመኑን ያማከል ቤተ መዘክር በማደራጀት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ፕሮጀክት በሚገባ ሲጠናቀቅ ቱሪስቶች ገዳማትን ብሎም ሀገርን ሊጎበኙ ሲመጡ የቤተክርስቲያንን፣ የሀገርን ቅርስን፣ታሪክና ባህል የሚጎበኙበትና የሚማሩበት የተዋጣለት ፕሮጀክት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት ዘርፈ ብዙ የሆነ በአራት አይና አባቶች የሚሰጡ የክህነት፣ የአቋቋም፣ የዜማ፣ የቅኔ ወዘተ ስልጠናዎችን በአብነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ይወስዳሉ፡፡የካህናት ሁለገብ ማሰልጠኛ ተቋም አንድ ካህን ዘመኑን ለመዋጀት በሚያስችለው መንገድ ሁለገብ ሆኖ እንዲዘጋጅና በቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና ማኔጅሜንት ብሎም በሕዝብ ግንኙነት በኩል ውጤታማ ሥራ ማስመዝገብ ይችል ዘንድ ብቁ የሚያደርገውን ስልጠና የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡ ካህናት በማሰልጠኛው በሚቆሙበት ጊዜ የሚያስፈልጋቸውን የመጠለያ፣ የምግብ፣ የትምህርት ቁሳቁሶችን ይዘጋጅላቸዋል፡፡ ከማሰልጠኛው የሚመረቁት ካህናት የነገዋ ቤተ ክርስቲያና መልካም የሆን ክርስቲያናዊ የክህነት አመራር እንዲኖራት፣ ብሎም ምእመናን በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ላይ ሙሉ እምነት እንዲኖራቸው ማድረግ የሚችሉ ብቃት ያላቸው ካህናት እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
በጽርሐ ጽዮን ከሚገነቡት አንዱና አይነተኛው ተቋም የግዕዝ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ይህ ተቋም በውስጡ የግዕዝ ቋንቋን ብሎም ዘመናት ተሻጋሪ የሆኑ ትሩፋቶችን ለማሳደግና ለማበልጸግ የሚያስችል ሲሆን በተገቢው መንገድ ተቀርጾ በሥራ ላይ ሲውል አስፈላጊ ተቋማዊ አደረጃጀት የሚኖረው ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ግዕዝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለቅዳሴ ሥርአት የምትገለገልበት ቋንቋ ሲሆን ይህ ቋንቋ የሚገለገልባቸው የግዕዝ ፊደላት በአፍሪካ ብቸኛ የሆነ የፊደል ሥርአት ነው፡፡ ይህን በመገንዘብ የጽርሐ ጽዮን ፕሮጀክት በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነ የግዕዝ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ ከዚህ ዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ምሁራን በትምህርት ተቋማት ውስጥ ግዕዝን የሚያስተምሩ፣ ምርምርን የሚያካሂዱ፣ ቋንቋውን የሚያሳድጉ፣ የግዕዝ ቋንቋ አምባሳደር የሚሆኑና ለቋንቋው ማደግ አስፈላጊውን እገዛ የሚያደርጉ ምሁራን እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
እነዚህን ተስፋ ሰጭ ፕሮጅክቶች ለመደገፍ አሁኑ ይርዱ
ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የእምነት ሥርዓት ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው የጌታችን የአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት በየአመቱ በጥር 11 ተከብሮ ይውላል፡፡ ይህ በዓል በባህር ዳር ከተማ እንደ ከተማው ታላቅነትና እንደ በዓሉ ክብር ደምቆ ይከበር ዘንድ ታቦታት የሚገናኙበትና የጥምቀቱ ሥርዓት የሚከበርበት ቦታ በጥሩ ሁኔታ ተሰርቶ የቤተ ከርስቲያኗን ክብር ባማከለ መንገድ እንዲጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ የተመረጠውን ቦታ በትክክል አስተካክሎ ሥራ ላይ ማውል የጽርሐ ጽዮን ፕሮጀክት ከሚያቅፋቸው ፕሮጀክቶች አንዱ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምትታወቅባቸው ሀብታቶቿ መካከል ዋነኛው ለብዙ መቶ አመታት ጠብቃ ያቆየቻቸው ድርሳናትና መጻሕፍት ናቸው፡፡ በሌላው አለማት የማይገኙ ዶክሜንቶችና ጽሁፎች በገዳማትና በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን መጻሕፍትና ድርሳናት የቤተ ክርስቲያናንና ሌሎችንም የአለም ጥበባት አምቀው የያዙ ናቸው፡፡ ስለህክምና፣ ስለማዕድናት፣ ስለስነጠፈር፣ ስለከዋክብት፣ ስለትውልዶች ወዘተ አብዝተው የሚተርኩ ጽሁፎች የያዙት ጥበብ ለተማሪዎች፣ ለምሁራን፣ ለሀገር ቤትና ለአለም አቀፍ ተመራማሪዎች ተጠብቀው የሚቆዩትና ሲፈለጉ የሚገኙት በተደራጀ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ነው፡፡ ይህ ተቋም ዘመናዊነትን በጠበቀ መንገድ የሚደራጅ ሲሆን ዘመኑ በሚፈቅደው መንገድ የኢንፎርሜሽን ሳይንስ ጥበብ በሚፈቅደው መንገድ ተሰርቶ ጊዜውን የሚዋጅ ቤተ መጻሕፍት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
ይህ በአሁኑ ሰዓት በግንባታ ላይ የሚገኘው የጽርሐ ጽዮን ፕሮጀክት አካል በአይነቱ ለየት ያለ ዘመናዊ የሆነ የቤተ ክርስቲያን ህንጻ ነው፡፡ ይህ ህንፃ በይዘቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የአሰራር ይዘትና ውስጣዊ ውበት የጠበቀ ሲሆን በውስጡ ባለሁለት መቅደስ ሆኖ የሚሰራ በእያንዳንዱ መቅደስ ቢያንስ እስከ አምስት መቶ ም ዕመናንን በአንድ ጊዜ ሊይዝ የሚችል ነው፡፡ ህንፃው ከአየር ላይ ሲታይ በመስቀል ቅርጽ የተቀረጸ ሲሆንምዕመኑ በአጸደ ቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር ግቢ ውስጥ በሚኖርበት ጊዜ ጠቅላላ ልቦናውንና ውስጠቱን ከፈጣሪው ጋር በሚያስተሳስር ልዩ መስህብ ይኖረው ዘንድ ታቅዶ የተወጠነ ነው፡፡