ጽርሐ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም
ይህ በአሁኑ ሰዓት በግንባታ ላይ የሚገኘው የጽርሐ ጽዮን ፕሮጀክት አካል በአይነቱ ለየት ያለ ዘመናዊ የሆነ የቤተ ክርስቲያን ህንጻ ነው፡፡ ይህ ህንፃ በይዘቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የአሰራር ይዘትና ውስጣዊ ውበት የጠበቀ ሲሆን በውስጡ ባለሁለት መቅደስ ሆኖ የሚሰራ በእያንዳንዱ መቅደስ ቢያንስ እስከ አምስት መቶ ም ዕመናንን በአንድ ጊዜ ሊይዝ የሚችል ነው፡፡ በመጀመሪያው ወለል ላይ አንደኛው መቅደስ የሚሰራ ሲሆን በሁለተኛው ወለል ላይ ደግሞ ሌላ ሁለተኛው መቅደስ ይሰራል፡፡ ህንፃው ከአየር ላይ ሲታይ በመስቀል ቅርጽ የተቀረጸ ሲሆን በቅርጸ መዋቅሩና በጠቅላላ በውጭና በውስጥ የሚቀረጹት ምስሎችና መልእክቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስን አስተምህሮት በሚያንጸባርቅ መንገዱ የሚሰሩ ሲሆን ምዕመኑ በአጸደ ቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር ግቢ ውስጥ በሚኖርበት ጊዜ ጠቅላላ ልቦናውንና ውስጠቱን ከፈጣሪው ጋር በሚያስተሳስር ልዩ መስህብ ይኖረው ዘንድ ታቅዶ የተወጠነ ነው፡፡ ይህ ህንጻ አልቆ በሥራ ላይ ሲውል በጠቅላላው በህንፃ መዋቅርነቱም ሆነ በአንድ ጊዜ ሁለት አገልግሎት ያለባቸው ሁለት መቅደሶችን በውስጡ በመያዙ፣ ብሎም በውጫዊና በውስጣዊ ይዘቱ በአይነቱ ሌላ ተመሳሳይና ወደር የሌለው ህንጻ ቤተ ክርስቲያን እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡