የካህናት ሁለገብ ማሰልጠኛ
ይህ ማሰልጠኛ ተቋም ካህናትን የተሟላ የቤተ ክህነት ትምህርትና አስተዳደር ስልጠና የሚሰጥበት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት ዘርፈ ብዙ የሆነ በአራት አይና አባቶች የሚሰጡ የክህነት፣ የአቋቋም፣ የዜማ፣ የቅኔ ወዘተ ስልጠናዎችን በአብነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ይወስዳሉ፡፡ እነዚህን ትምህርቶች ካህናቱን የተለመደውን አንድ ካህን ለቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎት ብቁ እንዲሆን በሚያስችለው መንገድ የሚያዘጋጅ ይሁን እንጅ ካህናቱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚሰጡ የአስተዳደር፣ የመንፈሳዊ ምክር፣ ብሎም የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን ለመስራት እንዲያስችላቸው ተጨማሪ ኮርሶችን እንዲሰጣቸውና ዕውቀታቸውን እንዲያዳብሩ ይጠበቃል፡፡ የካህናት ሁለገብ ማሰልጠኛ ተቋም አንድ ካህን ዘመኑን ለመዋጀት በሚያስችለው መንገድ ሁለገብ ሆኖ እንዲዘጋጅና በቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና ማኔጅሜንት ብሎም በሕዝብ ግንኙነት በኩል ውጤታማ ሥራ ማስመዝገብ ይችል ዘንድ ብቁ የሚያደርገውን ስልጠና የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡ ካህናት በማሰልጠኛው በሚቆሙበት ጊዜ የሚያስፈልጋቸውን የመጠለያ፣ የምግብ፣ የትምህርት ቁሳቁሶችን ይዘጋጅላቸዋል፡፡ ከማሰልጠኛው የሚመረቁት ካህናት የነገዋ ቤተ ክርስቲያና መልካም የሆን ክርስቲያናዊ የክህነት አመራር እንዲኖራት፣ ብሎም ምእመናን በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ላይ ሙሉ እምነት እንዲኖራቸው ማድረግ የሚችሉ ብቃት ያላቸው ካህናት እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡