የግዕዝ ዩኒቨርሲቲ
በጽርሐ ጽዮን ከሚገነቡት አንዱና አይነተኛው ተቋም የግዕዝ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ይህ ተቋም በውስጡ የግዕዝ ቋንቋን ብሎም ዘመናት ተሻጋሪ የሆኑ ትሩፋቶችን ለማሳደግና ለማበልጸግ የሚያስችል ሲሆን በተገቢው መንገድ ተቀርጾ በሥራ ላይ ሲውል አስፈላጊ ተቋማዊ አደረጃጀት የሚኖረው ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ግዕዝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለቅዳሴ ሥርአት የምትገለገልበት ቋንቋ ሲሆን ይህ ቋንቋ የሚገለገልባቸው የግዕዝ ፊደላት በአፍሪካ ብቸኛ የሆነ የፊደል ሥርአት ነው፡፡ ይህም የግዕዝ ፊደል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ ሥርአት የሚከናወንበት የግዕዝ ቋንቋ መክተቢያና የዜማ ማደራጃ የፊደል ሥርዓት ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያን በአለም መድረክ ከፍ አድርገው የሚያስጠሯት ከብዙ መቶ አመታት በፊት የተጻፉ ድርሳናት ተጠብቀው የቆዩት በግዕዝ ቋንቋ ነው፡፡ የግዕዝ ቋንቋ ያለውን አለምአቀፋዊ የሆነ የታሪክና የኃይማኖት ግብአት በማወቅ በአለም ዙሪያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በግዕዝ ቋንቋ የከፍተኛ ትምህርት ፕሮግራሞችን አዘጋጅተው ተማሪዎችን ያስመርቃሉ፡፡ በሐምበርግ ጀርመን፣ በፕሪንስቶን ዩንቨርሲት አሜሪካ፣ በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲና በሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች እንዲህ ያለ ከፍ ያለ ክብር የተቀዳጀው ግ ዕዝ ግን በትውልድ ሀገሩ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ትኩረትን አላገኘም፡፡ ይህን በመገንዘብ የጽርሐ ጽዮን ፕሮጀክት በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነ የግዕዝ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ ከዚህ ዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ምሁራን በትምህርት ተቋማት ውስጥ ግዕዝን የሚያስተምሩ፣ ምርምርን የሚያካሂዱ፣ ቋንቋውን የሚያሳድጉ፣ የግዕዝ ቋንቋ አምባሳደር የሚሆኑና ለቋንቋው ማደግ አስፈላጊውን እገዛ የሚያደርጉ ምሁራን እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡