የብጹዕ አቡነ አብርሃም መልዕክት
መልዕክተ ጴጥሮስ
እምጴጥሮስ ልዑከ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ለኅሩያን እለ ሀለው ውስተ በሐውርተ ቀጰዶቅያ ወጳንጦስ ወፍርግያ ወቢታንያ ወእስያ፤ በቀጰዶቅያ በጳንጦ በፍርግያ በቢታንያ በእስያ ላሉ ለተመረጡት ትድረስ፤
አምላካችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኃላ ቅዱሳን ሐዋርያት የወንጌሉን ብሥራት እንዲያዳርሱ በዓለም ሁሉ ከመዞራቸው አስቀድሞ እንደታዘዙት ለአንድ ዓመት በኢየሩሳሌም ያለችውን ቤተ ክርስቲያን እያስተማሩ ቆይተዋል፤ በዚህ ዓመትም በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል ፈጽሞ መላ ከፍ ከፍም አለ የሐርያት ሥራ ፮ ፥ ፯ በየዕለቱም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚገቡትን ያበዛላቸው ነበር፤ የሐርያት ሥራ ፪ ፥ ፵፯ ይልቁንም በእጢፋኖስ መሪነት የሚኖሩት ስምንት ሺኽ ክርስቲያኖች መደበኛ የሐዋርያት ተከታዮች የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ነበሩ።
ነገር ግን በእስጢፋኖስ ሞት ምክንያት ክርስቲያኖቹን አይሁድ በኢየሩሳሌም ከተማ እንዳይኖሩ ስላደረጓቸው በዓለም ተበተኑ የሐርያት ሥራ ፰ ፥ ፩ እግዚአብሔር ምክንያት ነበረው፤ በሀገሩ ሁሉ መበተናቸው ከአይሁድ ረድኤቱን ማራቁን እና ኃጢያት፣ አምልኮተ ጣዖት ወደ ስለጠነበት ሕዝብ ፊቱን ማዞሩን ወንጌል ወደ አልተሰበከበት ፈጥኖ እንዲደርስ ማድረጉ ያሳያል። የተበተኑትም ምዕመናን ዝም አላሉም በየደረሱበት ቦታ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይናገሩ ነበር ከሐዋርያት እንደተማሩት “ወውስተ ቤትኒ ኢኀደጉ ነጊረ ቃል እግዚአብሔር፤ በቤትም ውስጥ የእግዚአብሔርን ቃል ከመናገር አያቋርጡም ነበር” የሐርያት ሥራ ፬ ፥ ፴፪
ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ላይ የተዘራችው የቤተ ክርስቲያን ዘር ብዙ ፍሬ አፍርታ ባያት ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ሁለቱንም መልዕክታቶቹን ጻፈላቸው፤ ይልቁንም ከላይ የጠቀስናቸውን አምስት አሕጉር አድራሻ በማድረግ ይጽፍላቸዋል፤ በአካል ባያገኛቸውም በመንፈስ አይለያቸውምና። ቤተ ክርስቲያን ሕይወቷ አንድ መንፈስ ቅዱስ ነውና በሩቅም በቅርብም ብትሆን የተለያየች አይደለችም፤ አንድ ሕግ ወንጌል፣ አንድ አምላክ እግዚአብሔር፣ አንድ ራስ ክርስቶስ አላት። የአንድ የክርስቶስ አካል ስለሆነች በአንድ ራስ ሥር እንደተሰባሰቡ ኅዋሳት አንዱ ካንዱ የተለያየ ሊሆን አይችልም፤
ይልቁንም ቅዱስ ጳውሎስ “እኛስ የክርስቶስ ልብ አለን” ብሎ ሲናገር እንዴት ደስ ይላል? በመላው ዓለም ያለችው ቤተ ክርስቲያን አንድ ልብ ክርስቶስ ያላት ቋንቋዋም ፍቅር ነው፤ ቅዱስ ኤፍሬም ወደ ባስልዮስ በሄደ ጊዜ በቋንቋ የተለያዩ የሱርስት እና የጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ተናጋሪዎች ነበሩ ነገር ግን አንድ ልብ አንድ ክርስቶስ አላቸውና ከመግባባት አልተከለከሉም፤ በኋላም እስከ ዕለተ ሞት በአንድ ሀገረ ስብከት አብረው ነው የኖሩት፤ አገራቸው በሰማይ ነውና ቅዱስ ባስልዮስ ከዚህ ኑር ብሎ ኤፍሬምን ከሀገረ ስብከቱ ከፍሎ ሰጥቶ አኖረው።
በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያና በመላው ዓለም የሚትገኙ ወገኖቼ! ዛሬ ይህን ኀይለ ቃል የነሣሁላችሁ ያለ ምክንያት አይደለም በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት አዲስ እየተሠራ ያለውን የጽርሐ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም ምክንያት በማድረግ ይህን ድረ ገጽ መክፈታችን ይታወቃል፤ በዚህና በሌላም በኩል መረጃው የደረሳቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች ባደረጉት መንፈሳዊ ትብብር ምስሉን ያያችሁትን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ጀምረን በመሠራት ላይ እንገኛለን። ከዚህ ጋር አብረን በመላው ዓለም ለሚገኙ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርቲያናችን ልጆች የእግዚአብሔርን ቃል ባሉበት ስፍራ እንዲያገኙ በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት በመመሪያ ደረጃ ባቋቋምነው የሊቃውንት ጉባኤ እየተዘጋጀ፦
፩/ በትረ ኖላዊ ፬/ በወቅታዊ ጉዳዮች (ክብረ በዓላት)
፪/ ትምህርተ ሃይማኖት ፭/ በእንተ ገዳማት
፫/ የጥያቄዎቻችሁ መልሶች ፮/ የሀገረ ስብከቱ የልማት እንቅስሴ
በሚሉ ዐምዶች ሥር ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያንን ሊቃውንት በመጋበዝ በምሥል፣ በድምጽ እና በጽሑፍ ትምህርት ለማቅረብ ዝግጅታችንን አጠናቀናል።
ዘመኑ ያፈራውን የሥልጣኔ ውጤት ተጠቅመን ለሁሉም የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ቃል ማዳረስ የሚገባን ጊዜ ቢኖር አሁን ነው፤ በሰማይ በምድርም የመላ እግዚአብሔር በቃለ እግዚአብሔር ማጣት ምክንያት ከሰው ልብ ውስጥ መጥፋት የለበትም በተለይም ከሀገር ቤት ውጭ ያሉ በአብያተ ክርስቲያናት በካህናት ዕጦት ምክንያት የተጎዱ ወገኖቻችንን መጎብነት የዚህ መልዕክት አንዱ ዓላማ ነው፤ ቅዱስ ጴጥሮስ በእግር ላልደረሰላቸው የእስያና የገላትያ ምዕመናን እንደላከውም ላሬም በአካል ባናገኛቸውም በመንፈስ አንድ ነንና በየትም ስፍራ ምዕመናንን ማስተማር የሚገባ ጉዳይ ስለሆነ ይህን እንላለን።
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ሆይ! ዘመኑ እንደ ቀድሞው በየዋሕነት የምንመላለስበት አይደለም ሰላም ከምድራችን ላይ የራቀበት እርስ በእርሳቸውን የተለያየንበት፣ ተኩላዎች የበዙበት፣ ባላስፈላጊ ስህተት ሰውን ጠልፎ ለመጣል አስተማሪ ነን ባዮች የሚሯሯጡበት ዘመን ነውና “መንፈስ ሁሉ አትመኑ ይልቁንም መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ሁና እንደሆነ መርምሩ” ፩ኛ ዮሐንስ ፬ ፥ ፩ እንደተባለ መመርመር የምንችልበትን ትምህርት ከንፁህ የቤተ ክርስቲያን ልጆች መማር እንድትችሉ ይህን የትምህርት መድረክ ከፍተናል። ጥያቄዎቻችሁ ይመለሳሉ ገዳማቱን በመንፈስ ትጎበኛላችሁ፣ ወቅታዊ መልዕክቶችን እኔም እንደ እንደ አባትነቴ በበዓላትና በልዩ ልዩ ጉዳዮች የማስተላልፍላችሁን መልዕክቶቼን በዚህ መድረክ ታገኛላችሁ፤ የሀገረ ስብከታችንንም ልማታዊ እንቅስቃሴ እናስቃኛችኋለን። እንደ ቀድሞው የአባቶቻችን ዘመን ሁሉ አንድ ልብ አንድ ቃል ኖሮን የተዘጋጀልንን አንድ የእግዚአብሔር መንግሥት ለመውረስ የተጋን ሆነን ከተገኘን ለአባቶቻችን የገባውን ቃል ኪዳን እንደማያጥፍብን እምነቴ የፀና ነው። አምላከ አማልክት እግዚአብሔር ባላችሁበት ሁሉ ሕይወታችሁን ባርኮ በሃይማኖት ያጽናችሁ።
አምላካችን እግዚአብሔር ለሀገራችን ኢትዮጵያ እና ለዓለም ሁሉ ሰላምን ይስጥ።
አባ አብርሃም
የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
Add Comment