አምዶችን ለምን መረጥናቸው?
እነዚህ አምዶች ለምን መረጥናቸው?
የመረጥናቸው ዐምዶች በቁጥር ስድስት ሲሆኑ ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርቶች የምናስተናግድባቸው ቢጋሮች ናቸው። እነዚህ ፦
፩/ በትረ ኖላዊ
በትረ ኖላዊ ማለት የዕረኛ መጠበቂያ በትር ማለት ነው፤ በዚህ ዐምድ ስር የገሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ መልዕክትና ትምህርት አባታዊ ቃለ በረከት ይቀርብበታል የዐምዱን ስም በትረ ኖላዊ ማለታችንም ለዚህ ነው፤ የሙሴ በጎች የሙሴን በትር ከበው የለመለመ ሳር የጠራ ውሃ ሲመገቡ ይውሉ ስለነበር የሙሴን በጎች መጥፋት እና በአውሬ መነጠቅ አያሰጋቸውም ነበር እንዲያውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፲ ከቁጥር አንድ እስከ ፲፩ ባለው ክፍለ ትምህርት ምሳሌ አድርጎ ያስተማረው የሙሴን በጎች ስለመሆኑ የሐዲስ ኪዳን መምህራን ተርጉመው ይናገራሉ። ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም ሲሾሙ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን አርዌ ብርት የሚባለውን በትር አስጨብጣ ትሾማቸዋለች በሚንቀሳቀሱበት ሁሉ በትር ከእጃቸው አይለቁም የእረኝነታቸው ማሳያ ነው። ዛሬም በዚህ ዐምድ ስር በቅርብም በሩቅም ያሉ ምዕመናን ከመናፍቃን የሚጠበቁበትን ትምህርት የሚያስተላልፉበት ዐምድ ስለሆነ ይህን ስያሜ ተሰጥቶታል። ያጠፉም ይገረፍበታል፤ በሚገባ የሚሄድ ደግሞ ይጠበቅበታል።
፪/ ትምህርተ ሃይማኖት
በዚህ ርዕስ
፪.፩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምትቀበላቸው ዶግማና ቀኖና
፪.፪ ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያለን በማነጻጸር አንጻራዊ ትምህርት መለኮት
፪.፫ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የአኃት አብያተ ክርስቲያናትን ታሪክ
፪.፬ የሀገራችን ቅዱስ ሲኖዶስ የሚወስናቸው ዶግማዊና ቀኖናዊ ውሳኔዎች
፪.፭ እነዚህና ሌሎችም ከርዕሱ ጋር የሚዛመዱ ትምህርቶች በልዩ ልዩ መምህራን ይሰጥበታል
፫ የጥያቄዎቻችሁ መልሶች
በዚህ ርዕስ ከምዕመናን የሚነሡ ጥያቄዎችን የምንመልስበት ሆኖ ነገር ግን እንደ አስፈላጊነቱ ለምዕመናን መመለስ ያለበት የወቅቱ ጥያቄ ነው ብለን ካሰብን ጥያቄውን በማንሳት መልስ እንዲሰጥ የምናደርግበት ነው።
፬/ ወቅታዊ ጉዳዮች (ክብረ በዓላት)
በቤተ ክርስቲያን የሚከበሩ የጌታ የእመቤታችን የጻድቃን የሰማዕታት እንዲሁም የመላዕክት ዐበይት እና ንዑሳን በዓላትን አስመልክቶ ከመጻሕፍት ከመምህራን የሚነገሩ ታሪኮች ትምህርቶች ይቀርባሉ
፭/ በእንተ ገዳማት
ሀገራችን ኢትዮጵያ አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን በኋላም በሐዲስ ኪዳን የታላላቅ ገዳማት እና አድባራት መገኛ እንደ መሆኗ መጠን ታሪኮቿ የሚገኙት በገዳማትና በአድባራት መዳፍ ላይ ነው፤ ኢትዮጵያያ የሚያውቅ ትውልድ ገዳማቱን አድባራቱን ያውቃቸዋል፤ ገዳማቱን አድባራቱን የሚያውቅ ኢትዮጵያዊ ያሳውቃታል፤ ስለዚህም
፭.፩ ገዳማዊ ሕይወት እና ምናኔ፣ ምንኩስና
፭.፪ የታላላቅ ገዳማት ታሪክና ልማት በዚህ ርዕስ ስር ይዳሰሳሉ
፮ የሀገረ ስብከቱ የልማት እንቅስቃሴዎች
የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ቤተ ክርስቲያንን ከተረጅነት ለማውጣት የሚያስችል ከፍተኛ የልማት መነሣሣት ያለበት ሀገረ ስብከት በመሆኑ ቤተ ክርስቲያንን ከልመና ወጥታ ለማየት የሚሹ ምዕመናን በልማቱ እንዲሳተፉ እና የታሪክ ተካፋይ እንዲሆኑ ለማድረግ እንዲሁም በተለይም ሀገረ ስብከታችን የብዙ ሊቃውንት መገኛ ስለሆነ አብነት ትምህርት ቤቶችን እና መምህራኑን በወንበራቸው አጽንቶ ማቆየት እንዲቻል ቤተ ክርስቲያንም ተተኪ እንዳታጣ ለማድረግ ሀገረ ስብከቱ የሚሠራውን እየሠራ ምዕመናንም ድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግ የዚህ ርዕስ ዓላማ ነው።
እንግዲህ እግዚአብሔር ቢፈቅድልን ለቤተ ክርስቲያችን ልዕልና የሚሆነውን ሁሉ እያደረግን ከቀደሙት አባቶቻችን የወረስነውን ሃይማኖት ወደ ትውልዱ እንዲተላለፍ ለማድረግ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ሕያዋንና ሙታን ይገዛ ዘንድ በመጣ ጊዜ በምድር ላይ ሃይማኖትን ያገኝ ዘንድ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ድርሻውን ይወጣል።
እግዚአብሔር አምላክ ቅድስት ሀገራችንን በረደኤት ይጠብቅልን አሜን።
የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት
Add Comment