ጽርሐ ጽዮን ከየት እስከ የት?

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በ2000 አመታት ታሪኳ ብዙ ፈተና ውስጥ ያለፈች ሲሆን በ21ኛው ክፍለ ዘመን የገጠሟት ችግሮች በአይነታቸው የተለዩና የቤተ ክርስቲያኗን ሕልውና የሚፈትኑ ናቸው፡፡ በዚህ ሰዓት የቤተክርስቲያኗ ልጆች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለቤተ ክርስቲያኗ ዋቢ ጠበቃ እንድንሆን ይጠበቃል፡፡ በሌላ አነጋገር ለእምነታችን፣ ለቤተክርስቲያናችን ዘላቂ ደህንነት ብለን ዘመኑን እንድንዋጅና መስዋዕት እንድንከፍል የተጠየቅንበት ጊዜ ነው፡፡ ይኸንን ከምናደርግበት አይነተኛው መንገድ የቤተ ክርስቲያኗን ተልዕኮ የሚያራምዱ ስራዎችን በመስራት ይሆናል፡፡ ከዚህም ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ዋና ዓላማ የሆነው የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ለማጠናከር ዘመን ተሻጋሪ ተቋማት ለመገንባት አይነተኛ ሚና እንድንጫወት ይጠበቃል፡፡

ጠንካራ ተቋማት ቤተ ክርስቲያኗ ሐዋርያዊ ሥራዋን ለመሥራት የሚያስፈልጉ አይነተኛ መሳሪያዎች ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን ከዓላውያን፣ ከአረማውያንና ከመናፍቃን ከከሐድያን በመጠበቅ በየጊዜውና በየአቅጣጫው የሚሰነዘርባትን ፈተና በሃይማኖት ጽናት በመቋቋም፣ መንግሥተ እግዚአብሔርን በዓለም ዙሪያ ትሰብካለች፡፡ በድንበር፣ በዘር፣ በፆታ፣ በቀለም፣ በሀብት፣ በሥልጣን፣ በዕውቀት፣ በጉልበት፣… በመሳሰሉት ሳትለያይና ሳትገደብ ለምእመናን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ሰብአዊ አገልግሎትን ለማበርከት፣ የራሷን የምጣኔ ሀብት አቅም በማጠናከር በሰው ልጆች መካከል እኩልነት፣ ሰብዓዊነትና አንድነት እንዲጎለብት በሕዝብ አስተዳደር ሰላምና ፍትሕ እንዲሰፍን የበኩሏን አስተዋፅኦ ታደርጋለች፡፡ ይህንን ዘርፈ ብዙ አገልግሎቷን በሚገባና በብቃት ለመፈፀም ቤተ ክርስትያኗ ዘመን ተሻጋሪ ተቋማትን መገንባት ይኖርባታል፡፡

ከዚህ መሪ ራዕይና ተልዕኮ በመነሳት በዲያስፖራ የሚገኘው የጽርሐ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ አይነተኛ አላማው በኢትዮጵያ ባህር ዳር ከተማ ውስጥ የተጀመረውን ባለዘርፈ ብዙ ስትራቴጅክ ፕሮጀክት ተልዕኮውን ያሳካ ዘንድ የሚያስፈልገውን እርዳታ ማድረግ ነው፡፡ ኮሚቴው የሚሰራውን ሥራ ለመገንዘብ በባህር ዳር ሀገረ ስብከት ውስጥ የተጀመረውን የፕሮጀክቱን ራዕይና ተልእኮ ብሎም ድርጅታዊ መዋቅሩን መረዳት ያሻል፡፡

ፕሮጀክቱ በባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኝ ነው፡፡ የባህርዳር ሀገረ ሰብከት የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በሆኑት በብጹዕ አቡነ አብርሃም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የሚመራ ሲሆን በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሰረት ሀገረ ስብከቱ በባህርዳር ከተማና በአካባቢው ያሉትን ፹፭ በላይ የሆኑ አድባራትና ገዳማትን የሚያስተዳድር ነው። መንበረ ጵጵስናውም በባህርዳር ከተማ ነው፡፡ የቤተክርስቲያን ተቋማዊ ቅርጽ የተመሰረተችበት ዓላማና ተልዕኮ ለማስፈፀም የሚያስችል በመሆኑ፣ ሁሉም አካላት የተግባር ዕቅድ በማውጣት የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለማስፈፀም እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ይጠበቃል። በዚህም እሳቤ የባህር ዳር ሀገረ ስብከት የራሱን እቅድ በማውጣት እንቅስቃሴ እያደረገ ሲሆን፣ የቤተክርስቲያንን ተልዕኮ ለማሳካት አብያተ ክርስቲያናት በማሳነጽ፣ ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፣ የትምህርት ተቋማትን፣ ቤተ መዘክር፣ ቤተ መፃሕፍት ቤተ ነገድ የመሳሰሉትን ተቋማት በመገንባት፣ የቤተክርስቲያንን ተልዕኮና ተግባራትን ለማከናወን እንዲቻል ዝርዝር የትግበራ ዕቅድ አዘጋጅቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

የዚህ እንቅስቃሴ አካል ሆኖ ለመስራት ከተንቀሳቀሱት አካላት አንዱ በሰሜን አሜሪካ በተለያዩ ግዛቶች እንዲሁም በመላም ዓለም ያሉትን ምዕመናን በማስተባበር ትልቅ ተግባር ማከናወን ይቻላል በሚል እሳቤ በአሜሪካ ሀገር በቨርጂኒያ ግዛት ሕጋዊ ዕውቅናን ያገኘው ትርፍ አልባ የግብረ ሠናይ ድርጅት ነው፡፡ የዚህ ድርጅት አባላት የሆንን የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች  በሊቀ ጳጳሳችን መሪነት ያለንን እውቀት፣ ጊዜና ሀብት በማስተባበር, የተለያዩ የገንዘብ፣ የቴክኒክ፣ የሙያ እርዳታዎችን እያደረግን ሲሆን  ዘመኑ ያመጣቸውን ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሀገረ ስብከቱ መሪ እቅድ በአግባቡ ተግባራዊ የሚሆንበትን መንገዶች ለማፈላለግ ተደራጅተናል፡፡  በዘመናዊ አደረጃጀትና አፈጻጸም ሂደት ሀገረ ስብከቱ የተለማቸውን ዘመን ተሻጋሪ ተቋማት የመገንባት ቅዱስ ሀሳብ ለማሳካት ይቻላል በሚል ተስፋ ተነስተናል፣ ለዚህም “እኛ ተሰልፈናል፤ አምላካትን ያከናውንልናል፡፡” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ የነህምያን መርሆ አንግበናል።

ይኸንን ውጥናችንን በተግባር ለመተርጎም በአደረጃጀት በአመራር በስው ሀብትና በገንዘብ አቅም በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ተደራጅተን ከሀገረ ስብከቱ ጋር የተጠናከረ ድርጅታዊ ግንኙነት በመፍጠር እየሰራን እንገኛለን፡፡ እንደሚታወቀው ቤተ ክርስቲያናችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ሐዋርያዊ አገልግሎት እንድታበረክት በሁሉም ቦታ ያሉት ልጆቿ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናገሪ ሆነው መሰራት አለባቸው። እዚህ በዲያስፖራ የተመሰረተው የጽርሐ ጽዮንን ፕሮጀክት ለመታገዝ የተቋቋመው ኮሚቴም በዚህ መንፈስ የታነጸ ነው፡፡

ይህ የዲያስፓራው አስተባባሪ ኮሚቴ የሚሳተፍበትና በብጹዕ አቡነ አብርሃም መሪነት የታቀደው የጽርሐ ጽዮን ፕሮጀክት በዋናነት የሚያራምደው አላማ ይኸንን ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ተቋማትን መገንባት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከሚያቅፋቸው አይነተኛ ፕሮጀክቶች መካከል የሚከተሉት በአይነተኛነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

  1. የቤተክርስቲያን ህንፃ ሥራ ግንባታ (ጽርሐ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም)
  2. መንበረ ጵጵስና እና የሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ሕንፃ ግንባታ
  3. የካህናት ሁለገብ ማሰልጠኛ
  4. የመንፈሳዊና ዘመናዊ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት
  5. የግዕዝ ዩኒቨርሲቲ መገንባት
  6. ንዋያተ ቅዱሳት ማዘጋጃ
  7. ቤተ መዘክር
  8. ቤተ መጻሕፍት
  9. ቤተ ነገድ
  10. ጥምቀተ ባህር
  11. የመስቀል አደባባይ
  12. ሁለገብ አዳራሽ
  13. የመስቀል ሐውልትና ሕንፃ  ይገኙበታል፡፡

እነዚህን ፕሮጀክቶች ለማሰራት ብሎም ለሀገረ ስብከቱ ልማት ይውል የአማራ ክልል አስተዳደር 42,000 ሄክታር መሬት በታሪካዊው የባሕር ዳር ጣና ሐይቅ ትይዩ ለሀገረ ስብከቱ ያስረከበ ሲሆን በዚህ ቦታ ላይ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተጀምረዋል። በባለሞያዎች እንደተጠናው ይኽንን ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን 80,000,000.00 የኢትዮጵያ ብር እንደሚሆን ይገመታል፡

እንደዚህ ያሉ መልካም ጅምሮችን ለመርዳት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እስካሁን ድረስ ብጹእ አቡነ አብርሃም ወደ ሰሜን አሜሪካ በተጓዙባቸው ሁለት ታሪካዊ ጉዞዎች በተለይም በዋሽንግቶን ዲሲ፣ በአትላንታ፣ በካሊፎርኒያ፣ በቴኔሲ፣ በቴክሳስና በመሳሰሉት ቦታዎች ባደረጓቸው እንቅስቃሴዎች በኮሚቴው አስተባባሪነት ከ $500000 ዶላር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን ይኸው ገንዘብ ለፕሮጀክቱ ሥራ ይውል ዘንድ ባህር ዳር ለሚገኘው ኮሚቴ ተልኳ ሥራው እየተሰራ ይገኛል፡፡ ኮሚቴው ይኸንን ሥራውን በመቀጠል የተጀመሩት የተቋማት ግንባታ ጅምሮች ከዳር ለማድረስ እስከ መጨረሻው ድረስ በትጋት የሚሰራ መሆኑን ይገልጣል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን እየሱስ ክርስቶስ “በስሜ በምትሰበሰቡበት እኔ በመካከላችሁ እኖራለሁ” ብሎ በገባልን ቃል ኪዳን መሠረት ይህን እቅድ ለማስፈፀም ስንነሳ ከወዳጆቹ ዘወትር የማይለይ አምላካችን ይመራናል ይረዳናል ያስፈጽመናል በማለት በፍፁም እምነት ነው። ሃይማኖታዊ ግዴታችን እንድንወጣ ለጠራን ይህን ሐዋርያዊ አገልግሎት እንድንፈጽም በስሙ ስለሰበሰበን ለአምላካችን ክብር ምሥጋና ይሁን።

Add Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

I accept the Privacy Policy

Bitnami