የሊቀመንበሩ መልዕክት

ክቡራንና ክቡራት ምዕመናን ምዕመናት

በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሚሰራውን የጽርሐ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም ግንባታ ለማከናወን በብፁዕ አቡነ አብርሃም መሪነት የተጀመረው ፕሮጀክት በረጅም ጊዜ ስትራቴጂ፣ እቅድና ፕላን ተመርኩዞ ሥራውን ማቀላጠፍ ከጀመረ ውሎ አድሯል። ይህ ፕሮጀክት በአይነቱ ለየት ያለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ፣ ኣስተምህሮ፣ ብሎም ቤተ ክርስቲያኒቱ የደረሰችበትን ደረጃ ከግምት በማስገባት በደረጃው ከፍ ያለ ካቴድራል፣ የግዕዝ ዩኒቨርሲቲ፣ የሀገረ ስብከቱ  ጽ/ቤት፣ የካህናትና አገልጋዮች ማሠልጠኛ፣ የእንግዶች ማረፊያ፣ የአብነት ትምህርት ቤት፣ ቤተ መዘክር፣ ቤተ መጻሕፍት ብሎም የቤተ ክርስቲያኗን አገልግሎት የሚደግፉ የዕደ-ጥበብ ሥራ ማከናወኛ ተቋማትን ለመገንባት የታሰበ መጠነ ሰፊ ፕሮጀክት ነው።

ይህንን ፕሮጀክት በውጭ ሀገር በተለያየ ዓለማት የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቷ ምዕመናንና ሌሎችም ለቤተ ክረስቲያኗ ዕድገት የሚቆረቆሩ ሁሉ የሚቻላቸውን ድጋፍ አድርገው ሊያሳኩት የሚገባ የዚህ ትውልድ ሃላፊነት ነው። ይኸንን ሃይማኖታዊ አደራ ለመወጣት ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኙ ምዕመናንን ለማሰባሰብና ለፕሮጀክቱ የሚቻላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ ለማድረግ በሰሜን አሜሪካ፣ በዋሽንግቶን ዲ.ሲ ሜትሮ አካባቢ የሚገኙ ምዕመናን በአቡነ አብርሃም አሰባሳቢነት ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን የገንዘብ፣ የቴክኒክና የማቴሪያል እርዳታ ለማድረግ በኮሚቴ ተቋቁመው የተጀመረውን ጥረት በማገዝ ላይ ይገኛሉ።

ይህ የተቋቋመው ኮሚቴ በቨሪጂኒያ ግዛት ሕጋዊ ሰውነት ኑሮት የተቋቋመ ሲሆን፣ በIRS ትፍፋማ ያልሆነ ድርጅት 501(c)(3) የተቋቋመ ድርጅት ነው፥ በመሆኑም የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራውን ተጠሪነት እና ሃላፊነት ባለበት ሁኔታ በማሰባሰብ፣ ለድርጅቱ  በባንክ ኦፍ አሜሪካ ( 4350 4577 9055  ) የሂሳብ አካውንት እንዲኖረው በማድረግ ብሎም የተለያዩ ሃላፊነት የሚቀበሉ ንዑስ ኮሚቴዎችን በማቋቋም ተገቢውን እገዛ እያደረገ ይገኛል።

 ኮሚቴውም እለት ተዕለት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ሥራውን ላለፉት ሰባት ወራት ሲያከናውን ቆይቷል በመሆኑም እስከ አሁኑ ጊዚ ድረስ ለባሕር ዳር ሃገረ ስብከት ለሥራው የሚሆን ከምዕመናን በሰሜን አሜሪካ ከተሰባሰበ ገንዘብ በአጠቃላይ $155,000.00 ዶላር ወይንም $ 4, 477, 667. 84 የኢትዮጵያ ብር ለሥራው ማርኬጃ በመላክ ሥራውን እንዲፋጠን የበኩሉን ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ይህ ኮሚቴ ከዋሽንግቶን ዲ.ሲ. ሜትሮ ባሻገር በሌሎችም ግዛቶች የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን ለፕሮጀክቱ ለማነቃቃት፣ ብሎም ገንዘብ የሚሰባሰብበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ ይገኛል። ኮሚቴው የተሰበሰበው ገንዘብ በአግባቡ በደረሰኝ ገቢ እንዲሆን ፣ የሂሳብ ስራ በትክክል እንዲሰራ ፣ የኦዲት ቁጥጥር እንዲኖርና በጠቅላላው የሚሰበሰው ገንዘብ ለታሰበው ስራ እንዲውል በፕሮፌሽናል ባለሙያዎች እየታገዘ ስራውን ይሰራል። ይህ ኮሚቴ ፕሮጀክቱ በደንብ ተጠናቆ እስኪያልቅ ድረስ

ተጠሪነት ባለበት ሁኔታ ስራውን የሚያከናውን ሲሆን፣ በማንኛውም ጉዳይ ስለፕሮጀክቱ የሚነሱ ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ የሚችል መሆኑን በትሕትና ያረጋግጣል።

ይህ ፕሮጀክት የተሳካ እንዲሆን ለምታደርጉልን እርዳታ ሁሉ ከወዲሁ በልዑል እግዚአብሔር ስም ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር።

ከመንፈሳዊ ሰላምታ ጋር

አቤል ጋሼ፣ ሊቀ መንበር

በሰሜን አሜሪካ የጽርሐ ጽዮን ፕሮጀክት አሥተባባሪ ኮሚቴ

ልዑል እግዚአብሔር አምላክ ሃገራችን ኢትዮጵያን እና ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን በረድኤት ይጠብቅልን።

Add Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

I accept the Privacy Policy

Bitnami